< 1. እግዚአብሔር አዳምን ከመፍጠሩ በፊት አዳም እንደሚሳሳት ያውቃል/አያውቅም? እንደሚሳሳት ካወቀ ለምን ፈጠረው?
ወደጥያቄው መልስ ከመግባታችን በፊት ስለእግዚአብሔር ና ስለ ሰው ባሕርያት በጥቂቱ ማወቅ ያለብን ጉዳይ አለ። እግዚአብሔር የማይመረመር፡ ልዑልና ኃያል አምላክ ስለሆነ ስለራሱ የገለጠልንን ያህል ብቻ እናውቃለን እንጂ ሙሉ በሙሉ ልንደርስበት አንችልም። የሰው ልጅ በሁለንተናው ውሱን ነው። ዓይናችን የሚያይበት፡ ጆሮአችን የሚያደምጥበት፡ እጃችን የሚዘረጋበት…. ሁለንተናችን ገደብ አለው። ስለፈጣሪ ማወቅ አይደለም ስለፍጥረታት እንኳን ገና ያልደረስንባቸው ብዙ ጉዳዮች አሉ። ስለሆነም በአስተሳሰባችን ተነስተን የእግዚአብሔርን ሃሳብና አሠራር እንዲህ ቢሆን እንዲህ ይሆናል ብለን የራሳችን ግምት ልንወስድ አንችልም። ከውስንነታችን የተነሳ።
እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነው። ያለፈውን፡ የአሁኑን፡ የሚመጣውን ሁሉ ያውቃል። ዕውቀቱ ፍጹምና ገደብ የሌለው በመሆኑ አዳምን ከመፍጠሩ በፊት እንደሚሳሳት ያውቃል። በልጁ በክርስቶስ ሞት እንደሚያድነውም ያውቃል። ይህ ማለት ግን አዳም እንዲሳሳት ወስኖበታል ማለት አይደለም። አዳም በአሳቢ አእምሮው ተጠቅሞ ትእዛዙን የመጠበቅ/የመጣስ (ዕጸ-በለስን የመብላት/ያለመብላት) መብት የነበረው ነጻ ሰው ነው።
እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ የሚያከናውነው በዕቅድ ነው። ከዘላለማዊነቱ የተነሳ ይህ ዕቅዱ በሰዎች ምርጫና ድርጊት (ክፉም ይሁን ደግ) የማይለወጥ ነው። ነገሮች ሁሉ አስቀደመው በርሱ ዘንድ መታወቃቸው የሰዎችን ነጻ ፍላጎትና ድርጊት አይገድበውም። ማንኛውም ድርጊት ደግሞ ከርሱ ሥልጣንን ና ቁጥጥር ውጪ ነው ማለትም አይደለም። ልንመረምረው በማንችለው ሁኔታ በሰዎች ምርጫና ድርጊት ውስጥ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ ይፈጸማል።
እንግዲህ በአንድ በኩል የሰዎች ድርጊት በሙሉ የዘላለማዊ ዕቅዱ ማስፈጸሚያ አካል ሲሆኑ በሌላ በኩል ሰዎች በነጻነታቸው ለሚፈጽሙት ድርጊት ሁሉ ደግሞ ኃላፊነቱን ይወስዳሉ፡ ተጠያቂም ይሆናሉ።
አንድ መምህር እንዲህ ብሏል። ለሰው ልጅ የተሰጠውን ነጻ ፈቃድ እግዚአብሔርም ሆነ ሰይጣን አይጋፉትም። ይህ ማለት እግዚአብሔር በግድ ሰዎችን አያጸድቅም። ሰይጣንም በግድ ሰዎችን ኃጢአት አያሰራም። «ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል።» ያዕ ፩፡ ፲፬። እግዚአብሔር የመዳን (የሕይወት) ጥሪ፡ ሲያቀርብ ሰይጣን የኃጢአት (የሞት) ጥሪ ያቀርባል። ሰው ከሁለቱ አንዱን መምረጥ ይችላል። የመረጠውን ነገር ውጤት ግን ይቀበላል እንጂ አይመርጥም።
ስለሆነም ምንም እንኳ በዘላለማዊ ዕቅዱ እግዚአብሔር አዳም እንደሚሳሳት ቢያውቅም አዳም ግን የተሳሳተው በራሱ ሙሉ ነጻነት በወሰደው ምርጫ እንጂ እግዚአብሔር ያሳደረው አንዳች ተጽእኖ አልነበረም። እንዲያውም እንዳይሞት ባይበላ እንደሚሻለው መክሮታል። በዚያም ሆነ በዚህ የእግዚአብሔር ዕቅድ (አሳብ) ተፈጻሚ ነው።
ግን የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዕቅድ ምን ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ በሚነግረን መሠረት።
«ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን። በበጎ ፈቃዱ እንደወደደ በኢየሱስ ክርስቶስ ሥራ ለእርሱ ልጆች ልንሆን አስቀድሞ ወሰነን።---- በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው።» ኤፌ ፩፡ ፬ ፭ ፲
«እድፍ እንደሌለው እንደ በግ ደም በክቡር የክርስቶስ ደም እንደተዋጃችሁ ታውቃላችሁ። ዓለም ሳይፈጠር እንኳ አስቀድሞ ታወቀ።» ፩ጴጥ ፩፡ ፳።
እግዚአብሔር ዓለሙን ከመፍጠሩ በፊት በሰው ኃጢአት አንደሚበላሽ ስለሚያውቅ መድኃኒቱንም አስቀድሞ አዘገጅቷል። ዓለሙን ሳይፈጥር ቢቀር፡ ለርሱ የሚጎልበት አንዳች ነገር የለም። ሲጀመር የኛ መፈጠር ለርሱ የጨመረለት፡ የኛም አለመኖር ለርሱ የሚያስቀርበት አንዳች ነገር የለም።
ከጥያቄው ቀጥተኛ መልስ አንጻር ሊኖሩ የሚችሉት ሀሉት አማራጮች ናቸው።
F አዳምን እንደሚሳሳት አወቆ ባይፈጥረው እኛ አንኖርም፡ እርሱ ግን አለ። እንደነበረም ይኖራል። እዚህ ላይ ያበቃል።
F ነገር ግን ቢፈጥረውና ከወደቀበት ኃጢአት በልጁ በክርስቶስ ሞት ቢያድነው ይበልጥ እንድናውቀው አድርጎናል። ይህም የተፈጸመውና ያየነው አሳቡ ነው፡፡
ተጨማሪ ሃሳብ፡ ማብራሪያ ወይም ጥያቄ ካለ ከዚህ ጽሑፍ ስር comments የሚለውን በመጫን post comment በሚለው ሥር ማቅረብ ይቻላል።
ጌታ ቢፈቅድ ብንኖርም ሃሳብ ይሰጥበትና እንቀጥላለን። ካልሆነ ወደ ሌላ ጥያቄ እናልፋለን።
ይቆየን።
No comments:
Post a Comment
Give comments, አስተያየትዎን ይስጡ።